
የአፍሪካ የቡና ሳምንት በታላቅ ድምቀት በይፋ ተከፈተ!! 20ኛው የአፍካ ጉባኤም እየተካሄደ ነው::
የመጀመሪያው የአፍሪካ ቡና ሳምንት እና 20ኛው የአፍሪካ ባለልዩ ጣዕም የቡናዎች ማህበር ጉባኤና ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ በመካሄድ ላይ ይገኛል::
ጉባኤውና ኤግዚቢሽኑን በጋራ በመሆን ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን፣ የአፍሪካ ባለልዩ ጣዕም ቡናዎች ማህበር/AFCA እንዲሁም ኢንተር አፍሪካ ኮፊ ኦርጋናይዜሽን/IACO ናቸው ።
ከዛሬ ጀምሮ ለሚቀጥሉት አራት ቀናት በሚካሄደው ጉባዔ እና ኤግዚቢሽን ላይ ዓለም አቀፍ ቡና ገዥዎች፣ ቆዪዎች፣ ቡና አምራቾች፣ አልሚዎች, ላኪዎች, የዘርፉ ባለሙያዎች, የክልልና ፌዴራል መ/ቤቶች የስራ ሃላፊዎች, የምርምር ተቋማት እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ከ1000 በላይ እንግዶች በመሳተፍ ላይ ናቸው።
የግብርና ሚኒስትሩ ክቡር ዶክተር ግርማ አመንቴ በመክፈቻው ላይ እንዳሉት በአፍሪካ የቡና ኢንዱስትሪ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ቢኖሩም አሁንም አንዳንድ ችግሮች መስተዋላቸውን ተናግረዋል።
ከነዚህ መካከል የተለያዩ የቡና በሽታዎች፣ የበቂ ዝናብ እጥረት፣ የዓለም የቡና ገበያ በየጊዜው መለዋወጥ ተጠቃሽ መሆናቸውን አስረድተዋል:: እነዚህን ችግሮች በጋራ ለማለፍ በትብብር መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያም በአፍሪካ በቡናው ኢንዱስትሪ መስክ የሚገጥሙ ችግሮችን በትብብር ለማስወገድ በሚደረገው አህጉራዊ ጥረት የድርሻዋን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶክተር አዱኛ ደበላ በበኩላቸው ጉባኤና ኤግዚቢሽኑ በዘርፉ ያሉ ተዋንያንን ቅንጅት ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አስረድተው: ምርትና ምርታማነት ለመጨመር እንዲሁም በጥራት ለማምረት ከአርሶ አደሩ፣ በዘርፉ ካሉ ተዋንያን ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህን መሰል አህጉራዊ ሁነት በኢትዮጵያ መካሄዱ ኢትዮጵያ በመስኩ ያላትን አቅም ለማስተዋወቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸው በአፍሪካ የቡና ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ተዋንያንን የበለጠ የሚያቀራርብ የልምድ ልውውጥ መድረክ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢንተር አፍሪካ ኮፊ ኦርጋናይዜሽን ዋና ጸሃፊ አምባሳደር ሶሎሞን ሩቴጋ በበኩላቸው የአፍሪካ ቡና ኢንዱስትሪ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ እያለፈ መሆኑን አብራርተዋል።
የቡና ምርት ላይ እሴት አለመጨመር፣ የአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም ቡናን በሚፈለገው ደረጃ ያለማምረት ችግሮች ከፈተናዎች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በቡናው ኢንዱስትሪ መስክ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት አህጉራዊ ቅንጅቶች ሊጠናከሩ ይገባል ሲሉም አመልክተዋል።
በርካታ የቡና ድርጅቶችም ምርቶቻቸውን አቅርበው በተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ እንግዶች እየተጎበኘ ሲሆን በከሰአት በኇላ በነበረው መድረክም የፓናል ውይይቶች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ::
